የብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ አጭር የህይወት ታሪክ
ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ (1891-1971) አንዱ የአማርኛ ቋንቋ አባት ተብለው ቢወደሱ ማጋነን አይሆንም። ይህም የተባለበት ምክንያት የአማርኛ ሰዋሰውን አስመልክቶ ባደረጉት ጥልቅ ምርምሮች እና በተቀናጀ መልክ የተዘጋጁ የአማርኛ ሰዋሰው መማርያ መጸሀፍትን በመጻፋቸው ነው። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት ተቀጥረው በተርጓሚነት በአዘጋጓጅነት እና በደራሲነት ባገለገሉበት ጊዜ ከ35 በላይ የሚሆኑ መፀሀፍት ለህትመት እንዲበቁ አድርገዋል። በዚህም መሰረት የአማርኛን ቋንቋ ከዘመናዊ እና ከኪነታዊ አነጋገር በማስማማት ላደረጉት የላቀ አገልግሎት ድርጅቱ በ 1964 ዓ.ም. የአማርኛ ስነ ጽሁፍ ሽልማትን ሰጥቷቸዋል ። ከዚህም በተጨማሪ እንደ መምህር፡ ርእሰ መምህር፡ በብሪታንያ ሶማሌላንድ እና በፈረንሳይ ሶማሌንድ መካከል የተፈጠረውን የድንበር ግጭት ለመፍታት ለሶስት አመታት (1924-1927) ያገለገለው ኮሚሽን አባል እና ዋና ፀሀፊ በመሆን አገልግለዋል። የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ፤ የህግ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዘዳንት እና አማካሪ በመሆንም ለሀገራቸው ሰርተዋል። ከለይ ከተቀሱትም ባሻገር የኢትዮዽያን ታሪክ በማጥናትና መፀሀፍ ቅዱስን ወደ አማርኛ በመተርጎም ስራ ላይ ያላሰለሰ አስተዋጽኦ አድርገዋል።